Blog 9. Thoughts on Economic Reform by Dr. Berhanu Abegaz (2015)

ኢትዮጵያ ከጠባብና ከአግላይ የኢኮኖሚ ስርዓት እንዴት ትገላገላለች?

ብርሃኑ አበጋዝ* 

ይህን ጥያቄ ባጥጋቢ ለመመለስ መጀመሪያ ያገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በመመርመር የችግሩን መንስዔ መረዳት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ አራት አይነት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትሥሥራዊ ችግሮች ያሏት ይመስለኛል። ከነዚህ ሁለቱ ለመረዳትም ሆነ ለመፍታት አንዱ እጅግ ከባድ ሲሆን ሌላው ደግሞ እጅግ ቀላልነት ያለው የፖሊሲዎች አፈጻጸም ችግር ስለሆነ ለዛሬ እንተዋቸው። የቀሩት ሁለቱ ግን ዛሬ የምዳስሣቸው ናቸው። ከነዚህም አንዱ ለመረዳት ቀላል ስማስወገድ ከባድ የሆነው “ሙጀሌያሙ የፖለቲካ ስርዓታችን” ነው። ሁለተኛው ደግሞ ለመረዳት ከበድ ቢልም መፍትሔው ግን ቀለል ያለው “የመዥገር ኢኮኖሚ ስርዓታችን” ነው።

ስለዚህ ብዙዎቹ የአገሪቱ መሰረታዊ ችግሮች ያን ያህል ውስብስብና ሚስጥራዊ ሳይሆኑ እንደአሳና እንደ ዉሃ የተጋረዱ ግልጽ-ነገሮች መሆናቸውንም መርሳት የለብንም። አንድ ሽማግሌ አሳ ሁለት ትንንሽ አሳዎችን ሲያልፍ “ልጆች፦ከመጣችሁበት አካባቢ ለመሆኑ የዉሃው ሁኔታ ምን ይመስላል?” ብሎ ይጠይቃቸዋል። እነሱም ዘግተውት ትንሽ እንዳለፉ አንዱ ጎረምሳ አሳ ሌላውን “ለመሆኑ ውሃ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀው ይባላል።

ለማለት የፈለግኩት ህዝቡ የሚጎድለው የችግሮቹና የመፍትሔዎቹ ግልጽነትን አለመረዳት ሳይሆን አቅምና ዘዴን ማግኘት ነው። እኛም አንዱ ልናበረክት የምንችለው እንደ እውቀታችን ፍሬያማ ሃሳቦችን በማቅረብ እንጅ ስለድህነቱ በማላዘን አይመስለኝም።

እንደኔ አስተያየት የአገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መቆርቆዝ ኣንኳሮቹ ታሪክ-ሰደድ ምክንያቶች ባጭሩ ሁለት ናቸው፦ 

  • ባንድ በኩል ያገሪቱ መልክዓ ምድር በውሃ እጥረትና በአፈር ይዘቱ [እንደ ኣውሮፓና ምስራቅ እስያ] ከፍተኛ ቁጥር ያለው የገዢ ክፍልን የሚደግፍ ትርፍ ምርት ለማቅረብ አልቻለም። ስለዚህ ለዘመናት የቆየው የግብርና ስርዓት ‘ጉልታዊ’ እንጅ እንደሚባለው ‘ፊዩዳላዊ’ አልነበርም። ፊዩዳል ማለት የመሬት ከበርቴ ብቻ ማለት አይደለም፤ምርት አጎልማሽና ወደ ካፒታሊዝም መሸጋገሪያ መንገድ ጠራጊ ማለትም ነው።
  •  በሌላ በኩል በቀይ ባሕርና በአባይ ስትራቴጅያዊነት ምክንያት በኦቶማንና በግብዕ ተከበን ከሰፊው ዓለም ርቀን፥ በውስጥ የህዝብ ፍልሰቶች እየታመስን ራሳችንን ለውጭ ሃይሎች አጋልጠን እስካሁን ኖረናል። ገዥዎቻችንም እንደተራቡ አይጦች በተገኘችው ትርፈ-ምርት ላይ ሲረባረቡ ኖሩ። የውጭ እርዳታ ይጨመርበት እንጂ ስርዓቱ ዛሬም አልተቀየረም። ትርፍ ማምረት የሚችለው ገበሬውም ከሌለኝ ምኔን ይሰርቃሉ በሚል ትክክለኛ አስተሳሰብ በእጅ-ወደአፍ ኢኮኖሚ ኖረ፤የነቃው ልጁም ቄስነትን ወይንም ወታደርነትን መረጠ፤ የገሙ-ጎፋና የከፋ ከብት-አርቢ ወገኖቻችንም ‘ከብትን ማግበስበስ ዘርፎበላን ለመጋበዝ’ የሚል ዘይቤ አላቸው ይባላል። እውነታቸውን ነው።

በነዚህና በመሳሰሉ ምክንያቶች በጦርነት ተወሽቀን የኢንዱስትሪ አብዮት ባቡር እስካሁን ድረስ እንዳመለጠን ግልጽ ይመስለኛል። ስለዚህም ነው የፖለቲካ ባህላችን “የመንግስት አውታርን ማርከህ ክበር፤ ተሹመህ ብላ፤አስፈራራው በባንክና በታንክ” በሚሉት የዘርፎበላ አስተሳሰቦች ተቀርቅሮ የቆየው። የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ አሰላለፍ በቅንነትና በብልህነት ለማስተካከል እስካልቻልን ድረስ ከዚህ የተለየ የፓለቲካ ባህልን በሞራል ድስኩር ልናፈራው እንደማንችል ምርጫ-2007 የደመደመው ይመስለኛል።

ሁለተኛው ጥያቄ የዚህ ‘የምንልክን ግቢ ማርክ ካልሆነልህም ተገንጥለህ አዲስ ዘውድ ግዛ’ ፍካሬ-ማርያም ዘንድሮ መልኩ ምን ይመስላል የሚለው ነው። እንደኔ አስተያት በዘመነ- ወያኔ ስር-የሰደደው ‘የቀበሮ በግ-እረኝነት’ ስርዓት ሶስት ገጽታዎች ይታዩበታል። ገዢው ፓርቲ የአትራፊ ኩባንያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ባለቤት ነው፤ መንግስት የመሬት ፍጹማዊ ባለቤት ነው፤እንዲሁም በሶስቱም ድህረ-ጣሊያን መንግስታት የተተለሙ የእድገት ፕሮግራሞች በምርታማነት ሳይሆን በድጎማነት የተገደቡ ናቸው።

1ኛ) የገዥ ፓርቲ በመንግስት ኮርፖሬሽኖች ላይ ካለው የቀጥታ ቁጥጥር አልፎ የራሱን ኩባንያዎች ማስፋፋቱ የጭረታውን፥የፊናንሱን፥የፈቃዱንና፥ የታክሱን አፈጻጸም ከእኩላዊነትና ከዉድድራዊነት ወደ አድሏዊነት ከልሶታል። ይባስ ብሎም ገዢው ፓርቲ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጀሌዎቹን የሚደጉምበት ትልቅ ካዝና ስለሚያስፈልገው ህብረተሰቡን ጠልፎት ይገኛል።

2ኛ) የደርግ መንግስት ጭስኝነትን ያጠፋ መስሎት ርስትነትን አጠፋ። ለእኩላዊ ማከፋፈል አስፈላጊ ያልሆነ፥ ገጠሬው ትርፍ ኣምርቶ በነጻ ሸጦ የመክበር ዋስተናን ያልሰጠ፥ መሬትና ሰው ወደተሻለ ቦታ ወይንም የስራ መስክና ዘርፍ እንዳይሸጋገሩ አንቆ የያዘ የመሬት አዋጅ አስተናገደ። ወያኔ/ኢህአዴግም ይህን ቁጥጥራዊ የመሬት ስርዓት በደስታ ወርሶ እንኳን ኢንዱስትሪን ሊገነባ የምግብ ዋስትናን እንኳ እስከዛሬ ሊያጎናጽፈን አልቻለም። በዚች በዛሬ ቀን አስር ሚሊየን ህዝባችን ተርቦ-ውሎ ተርቦ-ያድራል።

3ኛ) ‘የቀንደኛ-ፓርቲ-መር’ ልማታዊነት ተብሎ የሚጠራው የወያኔ/ኢህአዴግ የልማት ስትራቴጂ ብዙ ዘርፍ ያለው ሌላው የእድገትና የዲሞክራሲ ማነቆ ነው። እንዱ ዘርፍ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” የሚል ሌኒናዊ ስም ተሰጥቶት ፓርቲው የሰፊው ሕዝብ ሞግዚትና አፈቀላጤ ሆኖ መቅረቡ ነው። አልፎም መንግስት የፓርቲው አገልጋይና ታዛዥ እንዲሁም ተቋማቱ በችሎታ ሳይሆን በታማኞች የተሰገሰጉ መሆናቸው ነው። ሶስተኛው ይህ የድጎማ ፖለቲካ ብዙ ገንዘብ ማፍሰስን ስለሚጠይቅ በተራ ሙስና ብቻ ሳይሆን በተቋማት ደረጃ ትርፍና ኪራይ ሰብሳቢ ኩባንያዎችን በማቋቋም እንዲሁም የመንግስትና የርዳታ ገንዝብን በማሸጋሸግ የሃገሪቱን ንብረት በህግ-አስመሳይ የዘረፋ ዘዴዎች ለደጋፊዎች መቸርቸር ለገዥ እድሜ ማራዘሚያ ቅድመ-ሁኔታ መሆኑ ነው።

ቀጥሎም የመደብ-ጦርነት መዶሻ ስለዶመዶመ የሶሻሊዝም ህብረ-ብሄር ግንባታን ትቶ በስሜታዊ የዘርና ሃይማኖት ክፍፍል ሕብረተሰቡን ማመስን መረጠ። ዶ/ር ሃይሌ ላሬቦ በቅርቡ ይህን የፓለቲካ ቅኝት “ከመደብ ጥላቻ ወደ አማራ ፍራቻ” በማለት የማትረሳ ስያሜ ሰጥተውታል።

የጎጣዊ ስርዓት ዘላቂነት የሌለው የኢኮኖሚ ዕድገትን ለጊዜው ቢያመጣም፥ ቋሚና ጠንካራ የእድገት ሞተርን ያቀፈ የእንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኣላመጣም፥ ሊያመጣም አይችልም። የአስተዳደሩም ዘዴ ብሄራዊ አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን ማዳከም 

ሶስተኛው ጥያቄ እነዚህ ተቋማትና ስልቶች ምን ጉዳት አስከተሉ የሚለው ነው። መልሱም፦ ስለሚያስፈልገው ጠንካራ ማእከላዊ የመንግስት ኣዉታር ከማቋቋም ይልቅ እንዳይሞት- እንዳይሽር ሆኖ የሚያነክስና ለቁጥጥር የሚያመች የጠለፋ መዋቅርን ዘርግቷል።

ስለዚህ ትልቁ ጥያቄ ለውጥ ማስፈለጉ ሳይሆን በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ምን አይነት የተቋምና የስልት ለውጦች ያስፈልጋሉ? እንዴትስ ይተገበራሉ? የሚሉት ናቸው። የምትጠራጠሩ ካላችሁ ሁለት ግንዛቤዎችን ላንሳላችሁ፦

  • ከ1870 እስከ 1970 ድረስ ኢትዮጵያ በነፍስ-ወከፍ ገቢ ቻይናን አሳምራ ትበልጣት ነበር። ባለፉት አርባ አመታት ግን ቻይና ችሎታዋንና እድሏን አቀናጅታ መጠቀች። አሜሪካንንም በብሄራዊ ኢኪኖሚ ግዙፍነት ከኋላ መጥታ ዘንድሮ በመቅደም በ1800 አ.ም. በአለም ኢኮኖሚ የነበራትን የብሄራዊ-መጠን አንደኛነት አስመልሳለች። ይህ ለኛ ትልቅ ተስፋ ሰጭ ነው።
  • እንዲሁም የፖለቲካ ወሬ-ወፍጮ እየተባለ የተሰለቀበት የኢትዮጵያ ወጣት ሳይወድ- በግድ ተስዶ ባርባ አመታት ውስጥ አዲስ ዲያስፖራ ቆርቁሮ ያሳየው አኩሪ የትምህርትና የኑሮ እድገት የችግራችን ስር-መሰረት ምን እንደሆነ በገሃድ አሳይቶናል።

በዚህ አኳያ አንድ ትልቅ ሹመት ያለው አሜሪካዊ ወዳጄ ከኢትዮጵያ በተመለስኩ ቁጥር የባለሁለት-ግጽታ ህዝብ መሆናችውን እየተገነዘብኩ እገረማለሁ፣ እስኪ ይህን እንቆቅልሽ ግለጽልኝ አለኝ። እኔም ይህ የታሪክ ላቦራቶሪ የሚያሳየን አሳፋሪ የድህነታችን ስር-መሰረቱ የተፈጥሮ ችሎታችን ውሱነት ሳይሆን የአስተዳደር ስርዓታችን ስንኩልነት ነው አልኩት።

በርግጥ አጥጋቢ መልስ አልተሰጠሁትም። ደግነቱ መፍትሄውስ አላለኝም። ከአቶ ‘በለው’፣ ከወ/ሮ ‘ብላው’ና ከጋሸ ‘ግዛው’ ሰንሰለት ወጥተን ወደ ሰርቶ-መክበር አትጊ ስርዓት እንዴት እንደምንሸጋገር እስካሁን ሚስጥሩ ገና አልተገለጸልንም። የዚህ ጥናታዊ ውይይት ጉባኤ ዋና አላማም በመፍትሄ ፍላጋ ላይ የሆነው ይህን ድክመት ለመቅረፍ ታስቦ ነው።

በቀረበው የመንደርደሪያ ወረቀት እንደምታዩት የስጠሁት የመፍትሄና የተሃድሶ መልስ ባጭሩ እንደሚከተለው ነው። ይህም አስተሳሰብ ስሜታዊ ሳይሆን ለ40 አመታት (ማለት ከመሬት አዋጅ ጀምሮ) ከትምርታዊና ጥናታዊ አለም ያገኘሁትን እውቀትና ግንዛቤዎች የሚያንጸባርቅ ነው። 

 

የኢኮኖሚ ስርዓቶች በሁለት መስፈርቶች ይገመገማሉ፦ አንዱ የሃብት ባለቤትነት (ማለት--መንግስታዊ፡ግላዊ፡ማህበራዊ) ሲሆን ዋናው ግን በሃገር ጉዳዮች ላይ ማን የወሳኝነት ስልጣን ይኑረው የሚለው ነው። በዚህ አንጻር ከኢትዮጵያም ሆነ ከስኬታማ ታዳጊ አገሮች የቀሰምናቸው ትምህርቶች እንደሚያሳዩን፦

1ኛ) አብዛኛዎቹ የአምባ-ዣንጥራሮች የሚባሉት የመንግስት የእርሻ፤የእንዱስትሪ፤ የንግድ፤ የአገልግሎትና የፊናንስ ኩባንያዎች ቢያንስ በጋርዮሽ ቢበዛ ደግሞ በግላዊ- ተናጠልነት እንዲሰሩና የገባያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ መደረግ አለበት። ይህም ማለት መንግስት የግል ባለሃብቱ የማይችላቸውን አስፈላጊ ኩባንያዎችን ፍጹም አያቋቁም ሳይሆን የዘመናዊ መንግስት ብኩር ተልዕኮው ውድድራዊነትን ማስፋትና የግለ-ኢኮኖሚውን መሪነትን ማጎልመስ መሆኑን ለመጠቆም ነው።

2ኛ) በህግ-አልባና በስርቆት የተቋቋሙት የገዢው ፓርቲና የግብረ-አበሮቹ ኩባንያዎች ያለምንም ጥያቄ (ነገር ግን በጥንቃቄ) ተዘጋጅተው በሃራጅ መሸጥ እንዳለባቸው ነው።

3ኛ) የገጠር እርሻና ግጦሽ መሬቶች በ1967 የመሬት አዋጁ ክፍፍል መሰረት ወደ ግል-ርስትነት መሸጋገር አለባቸው እላለሁ። የጎሳ አርበኞች ነፍጠኛን ሊያመጣብን፤ተራማጆች ደግሞ ገበሬውን መሬት-አልባ ሊያደርገው ነው ብላችሁ ሳታስቡ አልቀራችሁም። በኔ ግምት ይህ እርምጃ ‘የመሬት-ላራሹን’ መርህ በማክበር የመሃልና የደቡብ ክፍለሃገር ኢትዮጵያዊያኖች እንደ ሰሜኑ ህዝብ የርስት የመሬት ባለቤት ስለሚያደርጋቸው ነው።

በመሬት አዋጁ መሰረት ያልኩት አውቄ ነው። እንደምስታውሱት ‘አብዮት ጠላቶቿንም ልጆቿንም አብራ ትበላለች’ ይባል ነበር። የኛ አብዮት እርም-ሳትል ያልበላችው ወጣት ስለሌለ ወደፊት የወረስነውን ጎጆ በናቅን ቁጥር እሳት-እንልቀቅበት የሚለው ጮርቃና ስርዓተ-አልባዊ አስተሳሰብ ወደአገራችን ሁለተኛ እንደማይመለስ ተስፋ አለኝ። በነገራችን ላይ ዘንድሮ ደግሞ ‘አብዮት፣ ልጅና፣ የዘመኑ ቄሶች በሰው ግንዘብ ያለቅሳሉ’ መባል ተጀምሯል።

ይህ ቀልድ-ነክ አነጋገሬ ቁምነገርን ለማስመር ነው። በአብዮት ስም ህጉ የፈቀደላቸውን ድርሻ ለተቀሙ ዜጎች ሁሉ ምንም ቢዘገይም መሬታቸውን ወይንም ካሳቸውን መስጠት ፍትሕን ለማስከበር ብቻ ሳይሆን የቀምቶ-በላንና የቂም-በቀል ፖለቲካንም ለማክተም ይረዳል ብየ ስለማምን ነው። በተጨማሪም ርስቱን ሸጦ እንደመንጋ ወደመሸታ ቤት የሮጠ ህዝብ አይተን አናውቅም፤ብልሁ ገበሬ ሲራብ እንኳን ለወለድ-አግድ ይሰጣል እንጅ ርስቱን አይሸጥም። የመንግስት ብልጣብልጥ አቀንቃኞች እንደሚተነብዩት ሸጦ የፈለገውን ቢያደርግበትም እንኳ የራሱ መብትና ሃላፊነት ሆኖ መታየት አለበት። ሕዝብን ንቀን በኛ ራስን-ሿሚ እብሪተኝነት፣ ዱሮ ሶሻሊዝመን ዛሬ ደግሞ ሊበራል ዲሞክራሲን እንገነባለን ማለት በመሃይም እናቶቻችን አነጋገር ዘይቤ “ለመሆኑ ምን ቋንቋ ነው” ያስብልብናል።

ይህን ስል የመንግስት መሬት አይኑር ማለቴ አይደለም። ለህዝብ መዝናኛ የሚሆኑ፣ ትልልቅ ማእድኖችን የያዙና፣ የአግልግሎት ጣቢያዎች የሚሆኑ ቦታዎች ሁሉ መንግስታዊ ቢሆኑ መልካም ነው። አብዛኛዎቹ የእትዮጵያ ወንዞች የወዳጅ-ጠላት በመሆናቸው ካለብዙ ኢንቨስትመንት ሊከፈቱና መስኗዊ ሊሆኑ ስለማይችሉ መንግስት በባለቤትነት ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም እምብዛም አያከራክረንም።

4ኛ) የከተማ መሬትን በሚመለከት ሁለት አስተሳሰቦችን ማብጠልጠል ያስፈልጋል። በአንድ በኩል የህግ በላይነት በሰፈነባቸው አገሮች (ለንደን ከተማ አንድ ምሳሌ ነው) የከተማ መሬት የመንግስት ሆኖ በረዥም-ጊዜ ውል ባለቤቶች ሁሉ እንደልባቸው መሸጥ፣መለወጥና ማስተላለፍ ይችላሉ።

የኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ከዚህ ይለያል። አንደኛ በድህረ-ሶሻሊዝም ዘመን በአውሮፓና ሩስያ እንደተፈጸመው ያላግባብ የተወረሱትን የመመለስ ወይንም የመካስ ጥያቄዎች መስተናገድ አለባቸው። ሁለተኛ አስተማማኝ መንግስታትን እስክናፈራ ድረስ ጥበቃ እንዳለብን ተገንዝበን ዜጎች በትጉህነት ያፈሩትንና ያከማቹን ሃብት የፖለቲካ ጅቦች እንዳይቀሟቸው ለማድረግ ስለሚረዳ ነው። ለዲሞክራሲ ግንባታም ኢኮኖሚያዊ ይዘቶች ታላቅ አስተዋጽኦ ስላላቸው ለዜጎች አስተማማኝ የሃብት ባላቤትነትን ማልበስ ታታሪነትን ከማጎልመስ አልፎ ጭቆናን መካላከያ አቅማቸውን እንደሚገነባ የታዳጊ አገሮች ልምድ ያስተምረናል። የሊበራሊዝምም አንዱ ምሰሶም ይህ ይመስለኛል።

የእድገት ስልትን በሚለከት በወረቀቱ ላስረዳ እንደሞከርኩትና የምጣኔ-ሃብት ምርምሮች እንደሚያሳዩን ጥራት ያለው አማራጭ ስልት ሁለት አብይ ባህሪዎችን ማቀፉን ለማሳየት ሞክሬአለሁ፦

  •  አንዱ ምሰሶ የመንግስትና የግል-ሃብታም ክፍሎች በፉክክር ሳይሆን እጅና ጓንቲ ሆነው በአጋርነት መስራት ነው። ሁለቱም አንካሳ በሆኑባት ደሃ አገር ተደጋግፈው በልማት ላይ እንደመረባረብ በአስመሳይ ነጻ-ገባያ ጥላ ስር እንደጠላት መተያየታችውን ያቁሙ። ይህም የአፍሪካዉያን ትልቁ ድክመት ነው። የምስራቅ እስያ ልማታዊ ስትራቴጂ የሚባለውም ቻይናም በቅርቡ መከተል የጀመረችው ስልት በመሰረቱ አጋራዊ ነው። 
  • ሌላው ምሰሶ ያልኩት በገጠርና በከተማ የተሳሰረና በሁሉም ክፍለ-ግዛቶች እንደስጦታቸው የአቅም ግንባታ ድጋፍ እየተለገሳቸው የአግሮ-ኢንዱስትሪና የአገልግሎት ስራ ክፍፍሎችን ያቀፈ የእድገት ስልት መተለም ነው። ለዚህ የእድገት ስልት ታላቋ አዲስ አበባና አካባቢዎቹ ቁልፋዊ ሚና አላቸው።

በጠቅላላው ኢትዮጵያ ካለችበት የኢኮኖሚ አጣብቂኝ እንድትወጣ የሚያስችላት ማምልጫ አይኑን ለገለጠ ሁሉ የሚታይ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ቁልፉ የፓለቲካ ፈቃድኝነት ነው። ለበትረ-መንግስት ጠለፋ የተሰማራውን ገዥ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ለተመሳሳይ አገዛዝ ስርዓት የሚቋምጡትንም ተቃዋሚ ቡድኖች ከዚህ ዝቃጭ አስተሳሰብ እንዲጸዱ መምክርና ማስገደድ ነው። ባጭሩ ለህዝቡ በአለም-አቀፍ ኮንቬንሽኖት የተደነገጉት የግለሰቦች ነጻነቶች ይከበሩለት፤ ያላዋቂ ሳሚ አብዮታዊ ዲሞክራቶችና ልማታዊ ሃብታሞችም እባካች ተረረጋጉን እላለሁ። ሕዝቡ እፈለገበት ቦታ ሄዶ ይስራና በሰላም ይኑር፣በፈለገበት የስራና መስክ ይሰለፍ፣ የሃብት ባላቤትነቱም አስተማማኝ ዋስትና ያግኝ። እነዚህ በሰለጠነው አገር መሰረታዊ እሴቶች ናቸው።

ለዚህ ታላቅ ምኞት ፍሬያማነት የሚያስፈልጉን ለግንባታ አቅመ-ጠንካራና ለሕዝብ ታዛዥ መንግስት፣ ውድድራዊ የገበያ ስርዓት፣ ሰርቶ-ከባር ባለሃብቶችና፣ አገር-ውዳድ ዲያስፖራዎች ናቸው። እነዚህን ስልጣኔያዊ ተቋማት እንዴት እንደምንገነባቸው አዋቂዎቻችን ይምከሩበት። 

Tesfamichael MakonnenComment